ትላልቅ ዛፎች ተነቅለው በመውደቃቸው ቤቶች በከፊል ፈረሱ፤ መኪኖች ተደፈቁ፤ ተከታታይ የነፍስ አድን ስራዎች ተከናወኑ

በውሃ ማጣሪያ ጣቢያ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ለ1.9 ሚሊዮን ነዋሪዎች ውሃ የመቆጠብ ትዕዛዝ ተላለፈ… የተወሰኑ መንገዶች በጎርፍ ምክንያት ተዘጉ

የምስጋና ቀን (ቴንክስጊቪንግ) በዋለበት ሐሙስ ህዳር 26 ቀን ኃይለኛ የባህር ዳርቻ አውሎ ንፋስ ዋሺንግተን ዲሲን፣ ሜሪላንድን እና ቨርጂንያን የመታ ሲሆን፣ በብርቱው ንፋስ የተነቀሉ ትላልቅ ዛፎች በመኖሪያ ቤቶች እና በመኪኖች ላይ ወድቀዋል፤ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና የመንገዶች መጥለቅለቅ በማስከተላቸው በበዓሉ ወቅት በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

እንደ አካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ባለስልጣናት ገለጻ፣ በዕለቱ ከጠዋቱ 2:15 ገደማ በሜሪላንድ ግዛት ኬንሲንግተን ጋይገር ጎዳና (Geiger Ave.) በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ላይ ከ4 እስከ 5 ጫማ ውፍረት ያለው ግዙፍ ዛፍ ተከስክሶ ወደቀ። በዚህ አደጋ የቤቱ ጣሪያ እና የውጭ ግድግዳዎች ሲፈርሱ መኝታ ክፍሉ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። እንደ እድል ሆኖ የቤቱ ባለቤቶች በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ባለመሆናቸው ከአደጋው ተርፈዋል። በአቅራቢያው የምትኖር ሜሪ ጆ ሙን የተባለች ነዋሪ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ስትገልጽ "ቶርኔዶ የመጣ መስሎኝ ወደ ምድር ቤት (ቤዝመንት) ለመሸሽ ሞክሬ ነበር፤ ቤቱ ቃል በቃል ለሁለት የተሰነጠቀበት አሰቃቂ ትዕይንት ነበር" ብላለች። በሲልቨር ስፕሪንግ ሎምባርዲ መንገድም አንድ ትልቅ ዛፍ በመኖሪያ ቤት ላይ ወድቆ በቤቱ ውስጥ ተዘግቶባቸው የነበሩ ሁለት ነዋሪዎች በደረሱ የእሳት አደጋ ሰራተኞች በሰላም ድነዋል።

በቨርጂንያ ግዛትም ከፍተኛ ጉዳቶች ተከስተዋል። ከጠዋቱ 1:00 በኋላ በአርሊንግተን ካውንቲ ጆርጅ ዋሽንግተን ፓርክዌይ ወደ ደቡብ በሚወስደው መንገድ ላይ በመጓዝ ላይ በነበረ መኪና ላይ ዛፍ ወድቆ አሽከርካሪው በመኪናው ውስጥ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በእሳት አደጋ መከላከያ ሰራተኞች በተደረገው የነፍስ አድን ጥረት ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና አግኝቷል። በአሁኑ ወቅት ህይወቱ ከአደጋ ውጭ ነው። በፕሪንስ ዊሊያም ካውንቲ ሌክ ሪጅ እና ዴል ሲቲ አካባቢዎችም የዛፎች መውደቅ እና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሪፖርቶች በብዛት ደርሰዋል። የዶሚኒየን ኢነርጂ (Dominion Energy) የኤሌክትሪክ ኩባንያ "በኃይለኛ ንፋስ እና ከባድ ዝናብ ምክንያት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በመሰበራቸው እና ትላልቅ ዛፎች በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ በመውደቃቸው የመልሶ ማቋቋም ስራው ጥቂት ቀናትን ሊወስድ ይችላል" ሲል አስታውቋል።

በባህር ዳርቻ በሚገኙ ህንፃዎች ላይም ጉዳት ደርሷል። በሜሪላንድ ግዛት ኦሽን ሲቲ ከጠዋቱ 2:30 እና ከቀኑ 6:45 ገደማ በአትላንቲክ ጎዳና አካባቢ በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች (ኮንዶሚኒየም) ጨምሮ ቢያንስ የሁለት ህንፃዎች ጣሪያ በኃይለኛው ንፋስ ተነቅሎ ፍርስራሾቹ በአካባቢው ተበታትነዋል።

በዚህ አውሎ ንፋስ ምክንያት በተከሰተው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በቧንቧ ውሃ አቅርቦት ላይም አደጋ ተደቅኗል።

በሜሪላንድ ግዛት በሞንትጎመሪ ካውንቲ እና በፕሪንስ ጆርጅስ ካውንቲ ውስጥ በሚገኙ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለአጭር ጊዜ በመቋረጡ፣ የዋሽንግተን የከተማ ዳርቻ ንፅህና ኮሚሽን (WSSC Water) በስሩ ለሚገኙ 1.9 ሚሊዮን ነዋሪዎች ‘ለአስፈላጊ አገልግሎት ብቻ ውሃ እንዲጠቀሙ’ አስቸኳይ ጥሪ በማስተላለፉ በርካታ ቤተሰቦች የበዓሉን ሰሞን በጨለማና በእንግልት አሳልፈዋል።

በከባድ ዝናብ ምክንያት የተከሰተው የመንገድ መጥለቅለቅም የትራፊክ መጨናነቁን አባብሶታል። በደቡብ ምስራቅ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኙት ሳውዝ ካፒቶል ስትሪት እና ፊርዝ ስተርሊንግ ጎዳናዎች አካባቢ የፍሳሽ ማስወገጃው አቅም ከመጠን በላይ በመሙላቱ የዝናብ ውሃ ወደ መንገዱ በመመለሱ ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ በሁለቱም አቅጣጫዎች የሚደረግ የትራፊክ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል። በቨርጂኒያ ግዛት አሌክሳንድሪያ በሚገኘው ጆርጅ ዋሽንግተን መታሰቢያ ፓርክዌይም እንዲሁ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ መንገዱ በውሃ በመጥለቅለቁ በርካታ ተሽከርካሪዎች ተዘግተው የቆዩ ሲሆን፣ እንቅስቃሴው ዳግም የተጀመረው ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ገደማ ነበር።