ብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት እስከ 28ኛው ቀን ምሽት 4 ሰዓት (10:00 PM) ድረስ የጥንቃቄ ማስጠንቀቂያ አስተላለፈ… ቅዳሜና እሁድ ግልጽ እና ደስ የሚል አየር ይኖራል

በዋሽንግተን ዲሲ፣ በቨርጂኒያ እና በሜሪላንድ አካባቢዎች ከ27ኛው ቀን ምሽት ጀምሮ የበረዶ ጠጠር እና ኃይለኛ ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ነጎድጓዳማ ዝናብ እንደሚኖር በመተንበዩ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።

የአየር ሁኔታ ባለሥልጣናት "በሐሙስ ቀን የተከማቸው ሙቀትና እርጥበት በምሽት ሰዓት ድንገተኛ መካከለኛና ከባድ ነጎድጓዳማ ዝናብ ሊያስከትል ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል፤ በማከልም "ዋና ዋናዎቹ አደጋዎች ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ኃይለኛ ነፋሳትና ትላልቅ የበረዶ ጠጠሮች ናቸው" ብለዋል።

በተለይም በመካከለኛውና በሰሜን ምስራቅ ሜሪላንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ሊያተኩር እንደሚችል ይጠበቃል። የአየር ሁኔታ ባለሙያዎች ከአንድ ሳምንት በፊት በኩዊን አንስ ካውንቲ የተከሰተውን ቶርኔዶ በማስታወስ "በተለይም በሰሜንና በሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች በአዙሪት ንፋስ (Spin-up) ምክንያት የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ቶርኔዶ ሊከሰት የሚችልበትን ዕድል ማስቀረት አይቻልም" ሲሉ ገልጸዋል። ይህ አስከፊ የአየር ሁኔታ ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ይረግባል ተብሎ ይጠበቃል።

ብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት (NWS) ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ እንደ ፌርፋክስ፣ ላውደን፣ አርሊንግተን እና ፕሪንስ ዊልያም ባሉ 24 የቨርጂኒያ ካውንቲዎችና ዋና ዋና ራሳቸውን በቻሉ ከተሞች፣ እንዲሁም እንደ ሞንትጎመሪ እና ፕሪንስ ጆርጅስ ባሉ 14 የሜሪላንድ ካውንቲዎች ውስጥ የአየር ሁኔታ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል። የአየር ሁኔታ አገልግሎቱ ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ እስከ 28ኛው ቀን ምሽት 4 ሰዓት ድረስ ጸንቶ ይቆያል።

አርብ 28ኛው ቀን ከሰዓት በኋላም የቀዝቃዛ አየር ግንባር ሲንቀሳቀስ አልፎ አልፎ ዝናብ እና ነጎድጓድ ሊቀጥል ቢችልም፣ የአደጋው መጠን ከሐሙስ በእጅጉ ያነሰ እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህ ቅዳሜና እሁድ የሙቀት መጠኑ ወደ መካከለኛ 80ዎቹ ፋራናይት ዝቅ በማለት ግልጽና ደረቅ አየር የሚመለስ ሲሆን፣ ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ ግን የሙቀት መጠኑና እርጥበቱ ዳግም እንደሚጨምር ተተንብዮአል።